ከትላንት ተምረን ዛሬ ላይ ሆነን ለተሻለ ነገ እንትጋ
- Alem Nida
- Jun 18, 2020
- 1 min read
Updated: Jun 21, 2020
ከትላንት ተምረን ዛሬ ላይ ሆነን ለተሻለ ነገ እንትጋ
ትላንት ጥሩም ይሁን መጥፎ አሻራውን አሳርፎ አልፏል።የትላንት ጥሩ ተሞክሮ ጠብቀን ክፍተቶች አርመንና ለዛሬ ጥሩ ግብዓት ወስደን፤ትላንት ምንም ምክኒያት ይኑረው ዛሬ ላይ ነገን አሻግሮ ማየት ጊዜው የሚጋብዝ ነው ብዬ አምናለሁ። ባለፈው ለተፈጠረ ክፍተት ለሆነ አካል ተጠያቂ አድርገን እዛው ላይ ጊዜ መግደል ብልህነት አይደለም። የዚህ ስብስብ አላማም አይደለም። አላማው ይቅር ባይነት፤ እንዳይደገም መደገፍና አብሮ መሥራት፤ መደማመጥ፤መተባበር፤ መከባበር፤እራስን በራስ ለማገዝ መስራት፤ ከመንግስት የሚገባን በሠለጠነና በአብሮነት መንፈሥ ህጉን ተከትለን መጠየቅ፤የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ከኢትዮጵያነት ስነ-ልቦናና ሞራል የማይምታታ መሆኑን መረዳትና ማሥረዳት ስራችን ነው። በመሠባሠባችንና እያንዳንዳችን በምንችለው ጋኑን ለመደገፍ ከተባበርን የማንፈታው ቋጠሮ አይኖርም።
ከተሠባሠብን፤ ከተያያዝን፤ ለጋራ አላማና ለማህበረሰባችን ለተሻለ ነገር ዘይደን አብረን ከሠራን እና የማህበረሰባችንን እሴቶችና ጥሩ ተሞክሮዎች ቀምረን ከተጠቀምን ለውጥ እናመጣለን። ለሚሆነውና ለሆነው ሁሉ ከግላዊነት ወጥተን ድምዳሜ ከመድረሳችን በፊት መመርመርና መረዳት መሠረታዊ ነገር ነው። የእያንዳንዳችን ድርጊት፤የሥራችን ሚና፤ አስተሳሰባችን ተቀምሮ ከማህበረሰብ አልፎ በሀገር ግንባታ ላይ የራሱ አሻራ ያሳርፋል። በእያንዳንዱ ድርጊቶቻችን የመፍትሔ አካል ብንሆን የተሻለ ምርጫ ነው። ምን ተደረገልኝ ሳይሆን በምችለው ምን አሻራ አሳረፍኩ ይሁን ባይ ነኝ። የሌላ ሀሳብ ማክበር፤ መጥፎ ብለን የምንፈርጀው ሀሳብ ቢኖር እንኳን የሀሳቡ ባለቤት የተረዳበትና የሚያንፀባርቅበት መንገድ ትክክል መስሎት ይሆናል። ስለዚህ ሀሳብን በሠለጠነ መንገድ በሀሳብ መሞገት ብቸኛ መንገድ ነው። ሀሳቡን ካልተመቸህ/ሽ ሀሳቡን እንጂ ከሀሳቡን ባለቤት አገናኝቶ ወደ ቅራኔ መውሰድ የለብንም።

ጉርዳ
እንበርታ ረጅሙ ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራልና ዘድረሽ ቁርጡ