የጉራጌ ክልል ለምን አስፈለገ?
- Alem Nida
- Jun 23, 2020
- 5 min read

የጉራጌ ክልል ለምን አስፈለገ?
እንደ አንድ ግለሰብ፣ እንደ ሐገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እና እንደ አንድ የጉራጌ ማህበረሰብ ተወላጅ፤ የዘር ፖለቲካ፣ የዘር አከላለል እና ክፍፍል፣ በዘር ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ከመጥላት አልፌም በጽኑ ከሚቃወሙት፣ በተለይ ደግሞ የምንወዳት እና የምናከብራት በአባት እና አያቶቻችን ደም የተገነባችው ሐገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ማየት ከማይፈልጉት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነኝ። እውነት ለመናገር መላው የጉራጌ ህዝብ ማለት ይቻላል ይህንን አመለካከት ማንጸባረቅ ብቻም ሳይሆን ሆኖ የሚኖረው የለት ተለት ተግባሩ ነው። ለጉራጌ ከኢትዮጵያዊነት በላይ መገለጫ፣ ከኢትዮጵያዊነት በላይ ስብእና፣ ከኢትዮጵያዊነት በላይ ኩራት የለውም። ጉራጌ በእያንዳንዱ የእስትንፋሱ ቀናት ኢትዮጵያዊነትን ሆኖ ከሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን በዋናነት የሚጠቀስ ህዝብ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም።
አንድ ወንድማችን (መስፍን ሙሉጌታ) በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳለው፣ በኦሮሚያ የተወለደ ጉራጌ ኦሮሞ ሆኖ ነው የሚኖረው፣ በጎደር ወይም ባህርዳር ያለ ጉራጌ አማራ ሆኖ ነው የሚኖረው፣ በሱማሌ፣ በትግራይ እንዲሁም በሌሎች የሐገራችን አካባቢዎች የሚኖር ጉራጌ አካባቢውን መስሎ፣ ባህሉን ተላምዶ እና አክብሮ፣ ህዝቡን ቀርቦ እና ተዋዶ፣ እንዲሁም ከአካባቢው ተወላጅ ጋር ተጋብቶ እና ተዋልዶ፣ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ስራዎች ፈጥሮ እና የሚኖርበትን አካባቢን እያለማ እና እያሳደገ የሚኖር፤ ሰው አክባሪ፣ ተግባቢ፣ ስራ ፈጣሪ እና ከምንም በላይ ሰላማዊ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ነው፣ ጉራጌ።
የጉራጌ ህዝብ ክልል ሲጠይቅ ዘረኛ ሆኖ አይደለም። የጉራጌ ህዝብ የሚጠይቀውን የክልልነት ጥያቄ መደገፍ ዘረኝነትን መደገፍ አይደለም። ጉራጌ የጠየቀው የክልልነት ጥያቄን ለመደገፍ ፖለቲከኛ መሆን አይደለም፣ የመብት ጉዳይ ነው። ጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ሲጠይቅ የማንነት ጥያቄ እየጠየቀ አይደለም። ጉራጌ ከኢትዮጵታዊነት በላይ ማንነት የለውም። ጉራጌ መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነው፣ ከዛ ጉራጌ ነው። ጉራጌ በክልል ልደራጅ ሲል የትውልድ አካባቢዬን በራሴ ፍላጎት፣ ያለማንም ከልካይነት እንዳለማ ይፈቀድልኝ ነው ያለው። ጉራጌ ፍትህ ጎደለብኝ፣ በገዛ ሃገሬ እንደ የእንጀራ ልጅ መቆጠር እና የልማት ባይተዋር መሆን አንገሸገሸኝ ነው ያለው። ጉራጌ ጉዳዬን ለማስፈጸም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎሜትሮች መጓዝ ደከመኝ ነው ያለው። የጉራጌ ህዝብ መርጦ ባላስቀመጣቸው፣ ጉራጌ ክልልን እንኳንስ ሄደው ሊያዩት ቀርቶ ስለ ጉራጌ ምንም ያህል እውቀት እና ክብር በሌላቸው የመንግስት ካድሬዎች መመራት ይቅርብኝ ነው ያለው።
ስለ ጉራጌ ሲነሳ ብዙ ኢትዮጵያውያን መጀመሪያ የሚመጣላቸው፣ ታታሪ እና የስራ ሰው እንደሆነ፣ በመከባበር እና በመተሳሰብ የሚኖር ህዝብ እንደሆነ፣ ግርግር እና ጩኸት ያሉበት ቦታዎችን ትቶ ስራ ወዳለበት ቦታ የሚመለከት እንደሆነ፣ በገንዘብ አያያዙ የተዋጣለት እንደሆነ፣ በእቁብ እና በእድር እንዲሁም ሰላማዊ ህዝብ እንደሆነ እና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን ነው። እነኚህ አስተሳሰቦች መልካም ቢሆኑም ጉራጌው ስለ ጉራጌው የሚያስበው እነኚህን በዋናነት አይደለም፤ ይልቁንም ተባራሪ መረጃዎችን ብቻ የያዙ እና ስለ ጉራጌ በቂ እውቀት እና ግንዛቤ የሌላቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ናቸው።
ጉራጌው እና ስለ ጉራጌ ተገቢ እውቀት ያላቸው ሰዎች ደግሞ እጅግ በርካታ ነገሮችን ሊያስቡ ይችላሉ፣ ስለ ጉራጌ። እያንዳንዱን ነገር እዚህ ላይ ሊጠቀስ አይችልም፤ በትንሹ ግን፣ ቢያንስ ዋና ዋና የምላቸውን ለመጥቀስ ልሞክር። ጉራጌ በታሪኩ እና በባህሉ የስራ ሰው፣ እንደዛሬው ዘመናዊ ባንኮች እና አክስዮኖች በሌሉበት እስከዛሬው ድረስ በመላው ሐገራችን አገልግሎት ላይ ያሉት እንደ የእቁብ እና የእድር ስርዓቶች መስራች ህዝብ ነው። ዘመናዊ ዩኒቨርሲቲ እና ኢንጅነሪንግ ባልኖሩበት፣ ዘመናዊ ኢንጅነሮችን የሚያስደምሙ ውብ እና ዘመን ተሻጋሪ የመንገድ (ጀፎሮ) እና ግሩም የጎጆ ቤት (ጉየ ተኸራር) የአሰራር ጥበብ ባለቤት ነው። ጉራጌ የዘመናዊ ፌዴራሊዝም እና የዳኝነት ስርዓቶችን ሊወዳደሩ የሚችሉ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት እና የራስን በራስ የማስተዳደሪያ ወግ እና ስርዓት ባለቤት ነው። እንደዛሬው አለም አቀፍ የእናቶች እና የሴቶች በዓላት በማይታወቁበት ጊዜ አመታዊ የእናቶች ቀን (አንትሮሸት)፣ እና የሴቶች ቀን (ነቈ ተሰንቸ) ያከበረ፣ አሁንም የሚያከብር ህዝብ ነው። ጉራጌ እርስ በርስ የመረዳጃ፣ ድሆች እና አቅመ ደካሞች የመርጃ እና መደገፊያ፣ የታመመ መጠየቂያ እና የሞተ መቅበሪያ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ያሉት፣ እራስን በራስ የማስተዳደር እንዲሁም የነጻነት እና የእኩልነት ተምሳሌት የሆነ ህዝብ ነው።
እኔ ፖለቲከኛ ወይም አክቲቪስት አይደለሁም፣ የመሆንም እቅድ ወይም ፍላጎት የለኝም። ፍትሃዊ ጥያቄ ለመደገፍ ፖለቲለኛ ወይም አክቲቪስት መሆን አይጠበቅም፣ ጸሃፊም መሆን አያሻውም፣ ወይም የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን አያስፈልገውም። የፍትህ ጥያቄ ለመደገፍ የአንድ ብሄር አባል መሆንም የግድ አይደለም። ዛሬ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ያለአግባብ ተገደለ ተብሎ የአለም ሃያላን አገሮች የሚገኙ የጥቁር፣ የነጭ፣ የኤሺያ፣ የላቲኖ እና የተለያዩ የዘር ማንነት ያላቸው ሰዎች የፍትህ ጩኸት እያሰሙ ነው። ፍትህ ዘር አይመርጥም፣ ጎሳ አይጠይቅም፣ ትልቅ ወይም ትንሽ አይልም፣ የእድሜ ክልል አይከለክለውም፣ ፍትህ ጾታ አይመርጥም። ፍትህ ለመደገፍ የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል፣ የሐገር እንዲሁም የአህጉር ድንበር አገድብም። ጉራጌ ያቀረበው ጥያቄም የፍትህ ጥያቄ ነው፤ መሰል እና ሌሎች የፍትህ ጥያቄዎች
በማንም ይነሱ፣ በየትኛውም ብሄር እና አካባቢ ይጠየቁ መደገፍ ስልጡንነትም ሰብአዊነትም ነው። ጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ሲጠይቅ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ፣ ሌሎች ብሄሮችን ተለይቼ ልሂድ ማለቱ አይደለም፤ የትም አይሄድም። ጉራጌ ዞን የነበረው ክልል ይሁን፣ የአስተዳደር ነጻነት ይሰጠው፣ የራሱን ህዝብ እራሱ ያስተዳድር፣ አካባቢውን እንዲያለማ ይፈቀድለት ነው ያለው። ስለዚህ ይህንን የፍትህ ጥያቄው ጉራጌ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የሃገራችን ብሄሮች፣ ወንድሞቹ እና እህቶቹ ከጎኑ ሊቆሙ እና ሊደግፉት፣ ድምጹን ሊያሰሙለት ይፈልጋል። ፖለቲካ አላውቅም፣ መጻፍ አልችልም፣ ጉራጌ አይደለሁም፣ ገንዘብ ወይም ልዩ ሙያ የለኝም ሳይል ሁሉም በሚችለው እና እንደየ አቅሙ አስተዋጽዖ ሊያደርግ የግል ጥሪዬን አቀርባለሁ። የመላው የጉራጌ ህዝብም ጥሪ እንደሚሆንም አልጠራጠርም።
ጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ያቀረበው በዘር የመከፋፈል ፍላጎት ኖሮት አይደለም። ጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ያቀረበው ከሌሎች ብሄሮች ለመፎካከር አይደለም። ጉራጌ ከሌሎች ብሄሮች፣ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመከባበር፣ አብሮ በመብላት እንዲሁም የሚኖርበትን አካባቢ በማሳደግ በሰላም መኖርን የሚመርጥ፣ ብጥብጥ እና ሁከትን የሚጠላ እና የሚጠየፍ፣ በሐገራችን ከሚገኙ ብሄሮች ከሁሉም ጋር ተዋዶ እና ተከባብሮ አብሮ መኖር የሚችል እና የሚኖር ፍጹም ኢትዮጵያዊ ህዝብ እንደሆነ ጉራጌ በራሱ አንደበት ብቻም ሳይሆን በሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቹ አፍ መስማት የተለመደ ነው። ሁለት የጉራጌ ተወላጆች በእለታዊ ጉዳይ ተጣልተው ብጥብጥ ሲፈጥሩ የተመለከተ ኢትዮጵያዊ የመጀመሪያ ምክሩ፣ ‘ጉራጌ ሁኑ’ ነው።
ጉራጌ በክልል ልደራጅ ያለው ዛሬ አይደለም። ክልል ነበረም! ኢህአዴግ ሳይመሰረት በፊት ለረጅም ዘመናት ጉራጌ እራሱን በራሱ የሚያስተዳድር፣ እራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ወግ እና ስርዓት ያለው፣ ልጆቹን ሊያስተምርበት የሚችል ብቁ እና ሙሉ የሆነ ቋንቋ ያለው፣ እራሱን የቻለ የዳኝነት ስርዓት ያለው፣ ህዝቡን የሚደግፍበት እና የሚያሳድግበት የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አደረጃጀቶች የነበሩት እና ያሉት፣ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር ብቁ የሆነ እና ለሐገራችን ምሳሌ መሆን የሚችል ትልቅ ህዝብ ነበር፣ ነውም! ፍትህ ሲጓደል እና በደል ሲበዛ ማንኛውም ህዝብ የሌለበትን ባህሪይ ማምጣቱ አይቀርም። ምንም እንኳን ጉራጌ በዘር ክፍፍሉ ባያምንም፣ በዘር መካለሉ ባይደግፍም፣ በሐገራችን ነባራዊ ሁኔታ እና የሐገሪቱ መተዳደሪያ ህገ_መንግስት ጥቅም ላይ እስካለ እና እስካልተቀየረ ድረስ፣ ጉራጌ በክልል እንዲደራጅ መብቱም፣ አግባብም ነውና ጥያቄው በአፋጣኝ ሊመለስለት ይገባል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወንድሞች እና እህቶች (ሌሎች ብሄሮች) እንደሚደግፉት፣ ጥሪውን እንደሚያስተጋቡ፣ የፍትህ ጩኸቱን በመስማት እና በማሰማት እንደሚተባበሩት እና ከጎኑ እንደሚቆሙ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።
ጉራጌ በክልል ባለመደራጀቱ የሚቀሩበት ወይም የሚጎዳባቸው እና እስካሁንም እየተበደለ እና እየተጎዳባቸው ያሉ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። ለአብይነት ያህል የሚከተሉትን ልጥቀስ። የፍትህ እጦት/ የፍትህ መጓደል፣ የልማት እጦት/ የጉራጌ ህዝብ እራሱ እንዲያለማ እንኳን በሙስና እና በቢሮክራሲ ብዛት መጉላላት እና መከልከል፣ ከተለያዩ የሐገራችን ክልሎች (እራሱ ጉራጌ ተመድቦ ካለበት ደቡብ ክልል ጭምር) መፈናቀል፣ መደብደብ እና የንብረት ውድመት፣ በሐገራችን ፖለቲካ በቂ ዉክልና አለማግኘት፣ ቋንቋ እና ባህሉን መጠበቅ እና ማሳደግ አለመቻል፣ የአካባቢው ሰላም ማጣት እና በእጅ አዙር የእርስ በርስ የዘር ክፍፍል እንዲነሳበት መደረግ፣ የመንግስት መሰረተ ልማቶች አለመኖር/ የመንግስት ሰራተኞችን በቂ ደሞዝ ለመክፈል እንኳን የሚበቃ በጀት አለማግኘት፣ እየተበራከተ የመጣው የወጣቶች ስራ አጥነት፤ እንዲሁም ከምንም በላይ ደግሞ በክልል የመደራጀት ህገ_መንግስታዊ መብቱን መከልከል የሚሉትን ማንሳት እችላለሁ። በነገራችን ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ ጥናት ያደረጉ ሰዎች አሉ ወይም ይኖራሉ በዬ ተስፋ አደርጋለሁ፣ እነሱ ያዘጋጇቸውን የታሪክ መዝገቦች ማየት ተገቢ ነው። እዚህ የዘረዘርኳቸው ጉዳዮች እኔ የማውቃቸውን ብቻ ነው፣ ሁሉንም ለመዘርዘር መጽሐፍ ሊያስፈልግ ይችላል።
ጉራጌን የሚያውቅ፣ ስራ ፈጣሪነቱን፣ ስራ ወዳድነቱን እና አክባሪነቱን፣ በሄደበት ሁሉ አካባቢውን አልሚነቱን የሚያውቅ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ ጉራጌ ዞን ሄዶ ቢያይ በመገረም ቅንድቡን ሳያነሳ፣ ‘የጉራጌ ስም እና ዝናው የት አለ?’ ሳይል፣ በሚያውቀው ታሪክ ሳይጠራጠር ይመለሳል ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም የጉራጌ አካባቢ አለማም፣ አላደገም። ጉራጌ ማህበረሰብ ዉስጥ የሚገኙ አብዛኛው “የመንግስት” ተቋማት እና መሰረተ ልማቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሃኪምቤቶች፣ መንገዶች፣ የማብራት እና የውሃ አገልግሎቶች የተሰሩት በህዝቡ እና አዲስ አበባ በሚኖረው የጉራጌ ተወላጅ በተሰበሰበ የመዋጮ ገንዘብ ነው። እስካሁንም እየሆነ ያለው እንደዛ ነው፣ ይህንንም ለማድረግ የደቡብ ክልል ባለስልጣናትን ተለማምጦ እና ሙስና ከፍሎ ነው። እስከ አሁንም ድረስ በዞኑ በቂ የሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሉም። እስካሁንም እዚህ ግባ የሚባል የጤና ተቋም የለም። የኢንዱስትሪ ዞን የለም፣ አብዛኛው ስራ አጥ ወጣቱ ጊዜውን የሚያሳልፍባቸው የመዝናኛ፣ የእስፖርት እና የመማሪያ አገልግሎቶች የሉም። በእጅ ከሚቆጠሩ ኮሌጆች እና ከጥቂት አመታት በፊት ከተከፈተው ዩኒቨርሲቲ በስተቀር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሉም።
የጉራጌ ተወላጅ በትውልድ አካባቢው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሐዋሳ በመሄድ የደቡብ ክልል ባለስልጣናት ይሁንታን ማግኘት አለበት። ግቦ መክፈል አለበት፤ መመላለስ እና እንግልት ያጋጥመዋል። አብዛኛው ኢንቬስተር እንዲህ አይነቱን ዉጣ ዉረድ አይፈልግም፣ ስለዚህ ትኩረቶቹን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ያደርጋል። የጉራጌ
ህዝብ ፍትህ ለማግኘት እና የአስተዳደር ጥያቄ እንዲመለስለት እስከ ሐዋሳ መመላለስ ይጠበቅበታል። አብዛኛው ጊዜ ሳይመለስለት ይቀራል። በአንድ ጊዜ ጉራጌ ዞን ዉስጥ የምትሰራ አንድ ወዳጄ ደግሞ ያጫወተችኝ እስካሁን ይገርመኛል፣ ያሳዝነኛልም። “የጉራጌ ዞን ዉስጥ ከስንት አንዴ የሚገኙ፣ በውሎ አበል የሚሰሩ የመስክ ስራዎች ወይም ልዩ ልዩ ስልጠናዎች ሲኖሩ የዞኑ ተወላጅ እያለ የክልል መንግስት ከሌላ አካባቢ ባለሙያ ወይም ሰልጣኝ ይልካል። በጣም ነው ሞራል የሚነካው!” ብላኛለች።
እንግዲህ እኔ ዘርዝሬ ልጨርሳቸው የማልችላቸው በርካታ አስተዳደራዊ በደሎች በጉራጌ ማህበረሰብ ላይ ይደርሳሉ። የጉራጌ ማህበረሰብ በክልል እንድደራጅ ይፈቀድልኝ ያለው በምክንያት ነው፣ ህጉን ተከትሎ ነው፣ መስፈርቱን አሟልቶ ነው። መንግስት የጉራጌን ህዝብ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ህግ እና ህጉን ብቻ ተከትሎ እንዲፈቅድለት በግሌ እጠይቃለሁ፤ የመላው ጉራጌም ጥያቄ ነው።
ፈጣሪ ሐገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ!
የጉራጌ ክልል በአንድነት እና በልማት ወደ ፊት!
ድላርጋቸው ዳመስ